Yara International To Commence Construction For Potash Mining With 700mln Dollar
''ያራ ኢንትናሽናል '' የተባለ ኩባንያ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በሚደርስ ወጪ በዓፋር ዳሉል የሚገኘውን የፖታሽ ክምችት ለማምረት የሚያስችለውን ግንባታ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ።
የኩባንያው ዳይሬክተር ሚስተር ጆርጋን ስትንቮልድ ለኢዜአ እንደገለፁት ኩባንያው በኢትዮጵያ መንግስት በተደረገለት ጥሪ መሰረት ባለፉት ሶስት ዓመታት በዳሉል ረባዳማ ቦታ የፖታሽ ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ጥናት ሲያካሂድ ቆይተዋል።
ዳይሬክተሩ በዳሉል ረባዳማ ቦታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥራቱ ተወዳዳሪ የሆነ 500 ሚሊዮን ቶን የሚደርስ የፖታሽ ክምችት መኖሩን ጠቅሰው ኩባንያቸው ከማእዕን ሚኒስቴር በተሰጣቸው ህጋዊ ፈቃድና ቦታ ላለፉት ዓመታት የጥናትና የጉድጓድ ቁፋሮ ሲያካሂድ መቆየቱንም ገልፀዋል።
በተቆፈሩት አራት ጉድጓዶች ከ60 እስከ 200 ሜትር ጥልቀት ውስጥ የፖታሽ ክምችት መኖሩንና ይህም ከጨው ማእድን በመለየት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ጥራት ያለው የፖታሽ ምርት ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
በዳሉል የሚገኝ የፖታሽ ምርት በጥራቱ በመጀመሪያ ደረጃ ሊቀመጥ የሚችልና የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ የምርት ፍተሻ ስራ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ምርት ለመሸጋገር የሚያስችለው ግንባታ ለማካሄድ እስከ 700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚመድብ አስረድተዋል።
ኩባንያው በአከባቢው ያሉ አርብቶ አደሮች ቅድምያ የስራ እድል እንዲያገኙ ከማድረጉ በተጨማሪ ከሰመራ ዩኒቨርስቲ ጋር ግንኝነት በመፍጠር ተማሪዎች የጂኦ ሰርቨይ የተግባር ልምምድ እንዲያካሂዱ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በዓፋር ክልል ዳሉል ወረዳ የፖታሽ ማእድን በሚገኝበት የባዳ ቀበሌ አንዳንድ ነዋሪዎች እንደገለፁት ያራ ኢንተርናሽናል በአከባቢው ለሚኖሩ ወጣቶች ቅድምያ የስራ እድል በመስጠት ተጠቀሚ በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
Source: Ethiopian Radio and Television Agency (ERTA)
- 830 reads