Jump to Navigation

US-Based North Holdings To Build Cement Factory In Ethiopia

Published on: Sun, 2013-12-29 00:00
Cement factory image

ኖርዝ ሆልዲንግስ ኢንቨስትመንት የተሰኘው ኩባንያ በ800 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በአማራ ክልላዊ መንግሥት ደጀን ከተማ አቅራቢያ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፡፡

የኩባንያው ፕሬዚዳንት አቶ ተመስገን ቢተው ለሪፖርተር እንደገለጹት ኩባንያው በምሥራቅ ጎጃም፣ ደጀን ወረዳ ልዩ ስሙ መንዳ በተባለ ቦታ ለፋብሪካው መገንቢያ የሚሆን 250 ሔክታር መሬት ከአማራ ብሔራዊ መንግሥት ተረክቧል፡፡ ሊገነባ የታቀደው ፋብሪካ ሁለት የምርት መስመሮች እንደሚኖሩት፣ በዓመት 8.4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ፋብሪካውን የመገንባት ሐሳብ የተጠነሰሰው እ.ኤ.አ. በ2006 እንደነበረና የአዋጪነት ጥናቱ ተሠርቶ መጠናቀቁን አቶ ተመስገን ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው የፋብሪካውን ግንባታ የሚያካሂድና ማሽነሪዎች አቅርቦ የሚተክል ‹‹ኤፍኤስኤል›› የተሰኘ የዴንማርክ ኩባንያ ለመቅጠር ድርድሩን በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡

የፋብሪካው ግንባታ ወጪ 800 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ለፕሮጀክቱ የሚውል ብድር ተቀማጭነቱ ለንደን ከሆነ የኢንቨስትመንት ባንክ እንደሚገኝ አቶ ተመስገን አስረድተዋል፡፡

ከሲሚንቶ ፋብሪካው ግንባታ በተጨማሪ ሲሚንቶውን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያጓጉዝ የትራንስፖርት ኩባንያ እንደሚቋቋም የገለጹት አቶ ተመስገን፣ የሲሚንቶ ከረጢት ማምረቻም እንደሚገነባ ጠቁመዋል፡፡

የሲሚንቶ ፋብሪካው በኃይል አቅርቦት ራሱን እንዲችል በጎንደር ጭልጋ አካባቢ የድንጋይ ከሰል ማምረቻ እንደሚቋቋም ተናግረዋል፡፡ የተጠቀሱት ተያያዥ ድርጅቶች ወጪ ሲጠቃለል የኢንቨስትመንቱ መጠን 1.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ አቶ ተመስገን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ከ15,000 በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ለኖርዝ ሆልዲንግስ የኖራ ድንጋይ ምርት ፈቃድ ሰጥቶታል፡፡ የማዕድን ልማት ስምምነቱ በማዕድን ሚኒስቴርና ኩባንያው መካከል ባለፈው ሐሙስ ተፈርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቶሎሳ ሻጊና አቶ ተመስገን ናቸው፡፡ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ኩባንያው ለኖራ ድንጋይ ማምረቻ የሚሆን 24,513 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ የተሰጠው ሲሆን፣ የማዕድን ልማት ስምምነቱ ለ20 ዓመት የፀና ይሆናል፡፡

ኖርዝ ሆልዲንግስ ኢንቨስትመንት በአሜሪካ ዴልዌር በ12 ባለሀብቶች እ.ኤ.አ. በ2006 የተመሠረተ ኩባንያ ነው፡፡

Source: The Reporter



Main menu 2

Lambadi Software Developer P.L.C