Transport Bureau To Start New System That Solve Persistent City’s Transport Problem
ለአዲስ አበባ ከተማ የትራንሰፖርት ችግር ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል የፈጣን አውቶብስ ትራንስፖርት ፕሮጀክት በተግባር ላይ ሊውል ነው።
ትናንት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት በከንቲባው ጽህፈት ቤት አዳራሽ ባዘጋጁት የግማሽ ቀን ውይይት ላይ ነው ፕሮጀክቱ ይፋ የተደረገው።
ፕሮጀክቱ የከተማይቱን የትራንስፖርት ስርዓት የሚቀይር ፣ ቀጣይነት ያለው ፣ ዘመናዊና የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር እንደሚያስችል የተገለጸ ሲሆን ፥ በስራ ላይ ሲውልም ከተማይቱ የፈጣን አውቶብስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ተገልጿል።
አውቶብሶቹ በቴክኖሎጂ የረቀቁና በኮምፒውተር የሚታገዙ ሲሆን ፥ የራሳቸው የሆነ መስመርና ኮሪደር እንደሚኖራቸውም ነው የተጠቆመው።
በፕሮጀክቱ ዲዛይን መሰረት በአዲስ አበባ ዘጠኝ ኮሪደሮች ሲኖሩት ፥ ከዘጠኙ ኮሪደሮች መካከል የመጀመሪያው የሙከራ ትግበራ የሚሆነውና 12 ኪ.ሜ የሚሸፍነውም ከጎፋ ገብርኤል ተነስቶ በሜክሲኮና መርካቶ አድርጎ መጨረሻውን ዊንጌት የሚያደርገው ኮሪደር ነው ፤ ይህም የፓይለት ፕሮጀክት ኮሪደር እስከ ሰኔ 2006 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ፈጣን አውቶብሶቹ ስራ ሲጀምሩም በመስመራቸው በየሁለት እና ሶስት ደቂቃ ልዩነት አንድ ፌርማታ እንደሚደርሱና ተሳፋሪዎች አውቶብስ ለመጠበቅ ቢበዛ ከ4-5 ደቂቃ ብቻ እንደሚወስድባቸው ተብራርቷል ።
ፈጣን አውቶብሶቹ በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ በመሰማራት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ያግዛሉም ነው የተባለው።
ይህ የፈጣን አውቶብስ አገልግሎት ፕሮጀክት እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ እንደሚጠናቀቅና በአሁኑ ወቅት 50 በመቶ እንደተጠናቀቀ የሚነገርለትን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ በማገዝ ፤ የከተማዋን የትራንሰፖርት አገልግሎት ዘመናዊ ፣ ምቹ እና ቀልጣፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
Source: Fana Broadcasting Corporate (FBC)
- 2693 reads