KOS Co. Ltd. To Found Construction Materials' Plant In Ethiopia
ኬኦስ የተባለ የደቡብ ኮሪያ የግንባታ ግብአት አምራች ድርጅቶች ጥምረት ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ የግንባታ ዕቃዎችን በኢትዮጵያ ለማምረት የሚያስችለውን ዕቅድ ለከተማ ልማትና ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አቅርቧል፡፡
ለኢንዱስትሪው የመጀመሪያ ግንባታ ብቻ ከ50 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርግም ድርጅቱ በዕቅዱ አመላክቷል፡፡
ኬኦስ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የግንባታ ዕቃ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመክፈት በዓለም ገበያ የላቀ ስም ያተረፉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይ በቤቶች ግንባታና በተለያዩ የኮንስትራክሽን ዘርፎች ከፍተኛ ስራ እየሰራች በመሆኑ ፣የድርጅቱ የኢንቨስትመንት ጠያቄ የልማቱ ደጋፍ እንደሚሆን የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ ሀይለ መስቀል ተፈራ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 7 ዓመታት ቤት ፈላጊ ዜጎቿን የቤት ባለቤት ለማድረግ ሊገነቡ ለታቀዱት 7 መቶ ሺህ ቤቶች ጥራት ያለው የግንባታ ዕቃ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያድን ሚኔስተር ዴኤታው ኢንጅነር ሀይለመስቀል ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ልምድ ያካበተ በመሆኑ ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ለግንባታዎች ደህንነት ዋስትና ከመሆኑም በላይ ምርታቸውን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለሀገሪቱ እንደሚያስገኙም ሚኒስቴር ደኤታው ገልጸዋል፡፡
የኬኦስ ሀላፊ ሚስተር ኩዋንግ የም ሊ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ታሪካዊ ወዳጅነት በዘርፉ ለመሰማራት ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡
ኢንዱስትሪውን በሀገሪቱ ለመገንባት ሲታሰብ ትርፍ ለመሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጅ ሽግግርም እንዲኖር ለማስቻል መሆኑን ሚስተር የም ሊ አስረድተዋል፡፡
ኬኦስ በቻይና፣ በህንድ ፣በኳታር ፣በአርጀንቲና ፣ በሳውዲ አረቢያ እንዲሁም በተመሳሳይ በዱባይ የማምረቻ ኢንዱስትሪ የገነባ ሲሆን በ15 ሀገራት ደግሞ ምርቶቹን ያቀርባል፡፡
ድርጅቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ምርቱን በሚቀጥለው ዓመት እውን እንደሚያደርግ በዕቅዱ አስቀምጧል፡፡ ኩባንያው ፒፒሲ ቱቦዎችን በማምረት የመጀመሪያ ምርቱን ለገበያ አንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
ኬኦስ 10 የደቡብ ከሪያ የግንባታ ዕቃ አምራች ድርጅቶችን ያካተተ ስብስብ ነው፡፡
Source: Ethiopian Radio and Television Agency (ERTA)
- 1024 reads