Installation Of Rural Solar Power Projects 96 Percent Complete
ከመደበኛው የኤሌክትሪክ መስመር በርቀት የሚገኙ የገጠር ነዋሪዎች የመብራት ተጠቃሚ የሚያደርገው የፀሃይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ፕሮጀክት 96 በመቶ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የውሃ፣ መስኖና የኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በፕሮጀክቱም በመላው አገሪቱ የሚገኙ ከ150 ሺህ በላይ የህብርተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት 982 ኪሎ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ፕሮጀክቱ በአብዛኛው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በዚህም በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች፣ የተደራጁ ማህበራት፣ የትምህርትና አነስተኛና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ከዓለም ባንክና ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተገኘ በ209 ሚሊዮን ብር ብድር እየተካሄደ ያለው ፕሮጀክት ዘጠኙን ክልሎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ተናግረዋል።
የተከላው ሥራ እስከ ተያዘው ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ከ22 ሺህ በላይ የሶላር ሆም ሲስተም ቴክኖሎጂዎችን በመላው አገሪቱ ተተክሎ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በዚህም ስራ ከቴክኒክና ሙያ የተመረቁ ከ500 የሚበልጡ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ አድርጓል።
አገሪቱ በስፋት የሚገኘውና ብዙም ያልተሰራበት ከ5 ነጥብ 2 ኬሎ ዋት በሰዓትና በአንድ ስኩዌር ሜትር በቀን ማግኘት የሚችል በጸሃይ ሃይል ሊለማ የሚችል ሃብት እንዳላት ይታወቃል።
ይህንንም ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል በቅርቡ በተደረገው ጥረት 5 ሜጋ ዋት ያህሉን ሥራ ላይ በማዋል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አቶ ብዙነህ ቶልቻ አስረድተዋል።
ይህንን የፀሃይ ኃይል በመጠቀም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት መቻል በርቀት የሚገኙ ነዋሪዎች የተሻለ ኑሮ እንዲኖራቸው ከማስቻሉም ባሻገር አካባቢንና ተፈጥሮን የማይበከል የሃይል ምንጭ በስፋት በመጠቀም የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዘው ገልጸዋል።
አገሪቱ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መጨረሻ ከፀሃይ ኃይል ከ30 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨትና ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
Source: Ethiopian Radio and Television Agency (ERTA)
- 1389 reads