Gov't To Utilize Software, Fingerprinting To Verify Condominium Registrants
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በባለቤትነት በኢንሳ ሲያሠሩት የነበረው ሶፍትዌር በመጀመሪያ በአዲስ አበባ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ ከዚያም በክልሎች በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚሆን በከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የቤቶች ልማትና የመንግሥት ሕንፃዎች ግንባታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ ገብረ ጊዮርጊስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሚመለከታቸው የኢንሳ ባለሙያ ፕሮጀክቱ ከታሰበው ጊዜ የዘገየው በዕቃዎች እጥረት እንደነበር አሁን ግን ሲስተሙ ተዘርግቶ የአስፈላጊ መሣሪያዎች ዝግጅትም መጠናቀቁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች በሙሉ ባለሁለት ጣት አሻራና ፎቶግራፍ እንዲሰጡ የሚደረግ ሲሆን፣ አሻራው ባለሁለት ጣት እንዲሆን የተደረገው የበለጠ የማጣራት ሥራው ውጤታማ እንዲሆን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አንድ ወይም የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ሁለት ጊዜ መመዝገብ እንዲሁም ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞችን በመጠቀም ዕጣዎች ላይ ኢፍትሐዊ ዕድል ማግኘትን የመሰሉ ተግባራት በሶፍትዌሩ አማካይነት እንደሚቀሩ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባን የሚመለከት ሶፍትዌር በቀጣይ የንብረት አስተዳደርን እንዲሁም ብሔራዊ የመታወቂያ ካርድን ከሚመለከቱ ሌሎች ሶፍትዌሮች ጋር እየተያያዘ የሚሄድ ነው፡፡
ሶፍትዌሩን ተግባራዊ ለማድረግ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለሙያዎችን ማሠልጠን ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳ ኢንሳ ሶፍትዌሩን ያጠናቀቀ ቢሆንም፣ በተለያዩ ወረዳዎች የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎች መቼ አሻራ እንደሚሰጡ አለመወሰኑን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ከወራት በፊት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ በመቶ አሥራ ስድስት ወረዳዎች ላይ ተካሂዶ አሻራ የመስጠቱ ሒደት በምን ያህል ወረዳዎችና እንዴት ይካሄድ የሚለውም በአሁኑ ወቅት ያልተወሰነ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በጋራ የሚነጋገሩበት ይሆናል ተብሏል፡፡
የተመዝጋቢዎች አሻራ መስጠት ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ባንክን ጨምሮ በሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሶፍትዌሩን መሠረት በማድረግ ማጣራት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡
ኢፍትሐዊና አላግባብ (በማጭበርበር) የሚደረግ የኮንዶሚኒየም ቤት ምዝገባን ለመከላከል መንግሥት እንዲህ ያሉ አመዘጋገቦችን ለጠቆሙ ግለሰቦች ማበረታቻ የሚያደርግበትን አሠራር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
Source: The Reporter
- 1651 reads