Gibe Three Hydro Electric Project
የጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት
የጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት-[ዜና ትንታኔ] ከብርሃኑ ተሰማ(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ባሏት 12 ዋነኛ የውሃ ተፋሰሶች የኢነርጂ ልማት ልታካሂድበት የሚያስችላት 158ነጥብ 8ቢሊዮን ሜትር ኩብ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ሀብት አላት። ከዚህ ውስጥ 122ነጥብ ቢሊዮን የገጸ ምድር ውሃ ሀብት መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ይገልጻል። ሀብቱ አገሪቱ በኢነርጂው መስክ እያካሄደች ያለችውን ልማት በማንቀሳቀስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ይታወቃል።በዚህም 45ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ከራሷ አልፋ ለጎረቤቶቿ ከዚያም ተሻግራ ራቅ ያሉ አገሮችን ለመጥቀም እንደምትችል መገመት አያዳግትም። አገሪቱ ከንፋስ አንድ ሚሊዮን ሜጋ ዋትና ከጂኦ ተርማል ደግሞ ሰባት ሺህ ሜጋ ዋት የምታመነጭበት አቅም እንዳላትም ጥናቶች ያመለክታሉ። በመተግበር ላይ ባለው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅሟ ከሁለት ሺህ ሜጋ ዋት እምብዛም የበለጠ አይደለም። በኢትዮጵያ አሁን ሁለት ታላላቅ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ናቸው።የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትና የጊቤ ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እየተፋጠኑ ነው። ከንፋስ፣ ከጂኦተርማልና ከሌሎች አማራጮች ኃይል ለማመንጨት የሚደረገው እንቅስቃሴም እንደቀጠለ መሆኑን ሳይዘነጋ ማለት ነው። እንግዲህ ከነዚህ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መርነት ለመቀየር ወሳኝ ድርሻ ካላቸው ፕሮጀክቶች አንዱ የኦሞ ሸለቆን ተከትሎ በደቡብ ክልል በወላይታና ዳውሮ ዞኖች ውስጥ እየተገነባ ያለው የጊቤ ሦስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ይገኝበታል። ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ ከተማ በ400ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ከአምስት ዓመታት በላይ በግንባታ ላይ ይገኛል።1ሺህ870 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ፕሮጀክት እስካሁንም 65ከመቶ የሚሆነው ሥራው ተጠናቋል። ጠቅላላ ወጪው 32ቢሊዮን ብር የሆነው ፕሮጀክት፣ ከቻይና መንግሥት ከተገኘው 500ሚሊዮን ዶላር ብድር ውጭ ግንባታው የሚካሄደው ከመንግሥት በሚመደብ በጀት መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የኃይል አቅርቦቱን 10ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ እንደሚያስችልም መረጃው ያስረዳል። ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያና በኬንያ ያሉትን አርብቶ አደሮች ሕይወት ይጎዳለ በሚል እንዳይካሄድ ዓለም አቀፍ ዘመቻዎች የአካባቢ ተቆርቋሪ ነን በሚሉ ወገኖች ሲሰነዘርበት ቆይቷል። ሆኖም ጎረቤታችን ኬንያ ያለባትን የኃይል እጥረት ለመታደግ ከዚያ የሚመነጨውን ኃይል ለመጠቀም መፈለጓን ከመጠየቅና የጋራ ስምምነት ከማድረግ አልተቆጠበችም። የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ሰሞኑን ፕሮጀክቱን ለጎበኙት የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች እንዳስረዱት ኬንያ ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላት የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር መዘርጊያ ብድር ከዓለም ባንክ ተገኝቷል። ፕሮጀክቱ በአካባቢው ኅብረተሰብ በተለይም በኬንያው ቱርካና ሐይቅም ሆነ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ መፈናቀል እንደሚያደርስ ተደርጎ በከፍተኛ ደረጃ የተከፈተው ዘመቻ አካባቢውን ካለማወቅና ሐይቁ ያለበትን ደረጃ ካለመገንዘብ መመንጨቱንም ይናገራሉ። ከኬንያ በሁለት ዙሮች የመጡ ባለሙያዎች ፕሮጀክቱ ያሳድራል የተባለውን ተጽዕኖ ተመልክተው ችግር እንደማይከሰትና ጥቅሙ የጋራ መሆኑን ባደረጉት ጉብኝት ተገንዝበው መመለሳቸውን አስረድተዋል። የዓለምና የአፍሪካ ልማት ባንኮች የሚያውቋቸውና ፕሮጀክቱ በአካባቢና በማህበራዊ ሕይወት ዘርፎች ያለውን ድርሻ የሚመለከቱ 78 ጥናቶች መደረጋቸውንም አስታውቀዋል።ይህንኑ የሚመለከት አካል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት መቋቋሙንና ተጽዕኖውን የሚገመግሙ ጥናቶች እንደተደረጉም ኢንጂነር አዜብ አስታውሰዋል። በላይኛውና በታችኛው የሸለቆ ክፍሎች የሚኖረው ኅብረተሰብ በፕሮጀክቱ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ በአፍ መፍቻ ቋንቋዎቻቸው በተዘጋጁ ጽሁፎች መዘጋጀታቸውንና ከኅብረተሰቡ ጋር በ143 ቦታዎች ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል። የቱርካና ሐይቅ ከይዞታው 10በመቶ የሚሆነው ቀድሞ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበር ያስታወሱት ኢንጂነር አዜብ፣በአየር ንብረት ለውጥና በራሱ ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች መጠኑ እየቀነሰ መምጣቱንና ፕሮጀክቱ ጥቅም ላይ ባዋለው የኦሞ ወንዝ ሳቢያ የውሃ መጠኑ እምብዛም ለውጥ እንዳልታየበት ተናግረዋል። ''ሐይቁ ባልተመጣጠነ የውሃ መጠን ሲቸገር የነበረና አሁን አምስት ሜትር ያህል የመሸሽ አዝማሚያ እየታየበት ነው።ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ግን የውሃውን መዋዠቅ መጠን ወደ አንድ ሜትር ተኩል በመቀነስ የተመጠነ ውሃ ሁሌም እንዲያገኝ ለማድረግ ይቻላል'' ብለዋል። በሸለቆው የታችኛው ክፍል ወንዙ የሚያመጣውን ደለል በመመርኮዝ የሚከናወነው የእርሻ ሥራ አንድም ከመጠን በላይ በሚሆነው የውሃው መጠን ጎርፍ ተጠርጎ የመወሰድ፣ሌላም ለምርት የሚውልበት ሁኔታ እንደነበር ሥራ አስኪያጇ አስታውሰዋል። ይሁንና አስተማማኝ ባልነበረው የእርሻ ሥራ ይተዳደር የነበረውን ኅብረተሰብ ሕይወት ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ፤ፕሮጀክቱ በየዓመቱ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ውሃ እየለቀቀ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መቀየሱን አስታውቀዋል።ይህም የእርሻ ሥራቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው አብራርተዋል። ''ነዋሪዎቹ አስተማማኝ ባልሆነ ምርት ላይ ስለተሰማሩ የዓመቱን አብዛኛውን ጊዜ በምግብ ዕርዳታ የሚኖሩ ናቸው'' ያሉት ኢንጂነር አዜብ፣ነዋሪዎቹ አስተማማኝነት ከሌለው አኗኗር ወጥተው ዘላቂ ሕይወታቸውን ለመምራት የሚችሉባቸው ሌሎች አማራጮች መቅረባቸውን ገልጸዋል። ሸለቆው ለእርሻ ሥራ አመቺ ያለመሆን ብቻ ሳይሆን፤ለወባና ሌሎች በሽታዎች የተጋለጠ በመሆኑ ለኑሮ ምቹ እንደማያደርገው አስረድተው፣በፕሮጀክቱ በሚሰሩላቸው የመሠረተ ልማት ተቋማትና የሰው ኃይል በሚያስፈልጋቸው መደቦች ቅድሚያ አግኝተው በመቀጠር ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል። ፕሮጀክቱ በ246 ሜትር ከፍታ እየተካሄደና በዚህም ከዓለም ታላላቅ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አንዱ ለመሆን የሚያስችለው ሲሆን፣ እየተገነባበት ያለው ቴክኖሎጂም ለአገሪቱ የመጀመሪያው እንደሚያደርገው አመልክተዋል። ከግድቡ ሁለት ሚሊዮን ሜትር ኩብ አፈር የወጣለት ቁፋሮ በማከናወን ውሃውን ወደ ኃይል ማመንጫዎች የሚያደርሱ የታናል፣የሁለት ግድቦችና የኦሞ ወንዝ ድልድይ ሥራዎች ተከናውነዋል። የኃይል ማመንጫ ቤቶቹ ግንባታም ከ40 በመቶ በላይ መድረሱና የግንባታ ሥራውም በዘመናዊ መልኩ በተደራጀ የግንባታ ቁሳቁስ ማምረቻ ተደባልቆ እየተዘጋጀ ሥራው እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። እንዲሁም የኦሞ ወንዝ ሰው ሰራሽ ሐይቅ 15 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የሚይዝ ግንባታ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ከሐይቁ ወደ ኃይል ማመንጫ ውሃውን የሚያደርሱ ቁመታቸው ከአንድ ኪሎ ሜትር ያልበለጡ ሁለት ዋሻዎች እየተገነቡ መሆናቸውን አስረድተዋል። ''ፕሮጀክቱ የካርበን ጉዳትን በመቀነስና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል''ሲሉም ኢንጂነር አዜብ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በሳሊኒ ኮንስትራቶሪ ድርጅት ግንባታው የሚከናወን፣የቻይና ኩባንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭቱን፣ሁለት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቁጥጥር ሥራዎች የሚያከናወኑለት ሲሆን፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ደግሞ በፕሮጀክቱ ባለቤትነትና ተቆጣጣሪነት ነው። ፕሮጀክቱ ከ24 አገሮች የተውጣጡ የውጭ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከስድስት ሺህ በላይ ሰዎች መሰማራታቸውን ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል። እያንዳንዳቸው 187ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 10 የኃይል ማመንጫዎች(ተርባይኖች)ም ይኖሩታል። ፕሮጀክቱ ለአገሪቱና ለጎረቤት አገሮች ኃይል ከማቅረብ በተጨማሪ የአካባቢው ሕዝብ በአነስተኛ የመስኖ ሥራዎችና በዘመናዊ የዓሣ እርባታ በማሰማራት ተጠቃሚ ያደርጋል። ፕሮጀክቱ በሰኔ 2006 ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠናቀቅ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት በማሳደግም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከፕሮጀክቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዘገባው አመልክቷል። ከዳውሮ ዞን ሎማና ከወላይታ ዞን ኪንዶ ክዳያ ወረዳዎች የመጡት አቶ መሥፍን ጫፎና አቶ ዓባይነህ አልታዬ በሰጡት አስተያየት በፕሮጀክቱ ባገኙት የሥራ ዕድል ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት መብቃታቸውንና ፕሮጀክቱ ያለ ምንም ጥቅም ሲፈስ የነበረውን ውሃ ለአገር ጥቅም በመዋሉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የውሃ ሀብታችንን ለዕድገትና ለጋራ ጥቅም በማዋል ኢንዱስትሪን በማስፋፋት የአገሪቱ ሕዝብ ሕይወት ለማሻሻል እንደሚቻል ጅምሩ አመላክቷል።ፍጻሜውም እንደሚያምር አያጠራጥርም።
Source:-Ethiopa news agency
- 1497 reads