Jump to Navigation

Draft Law for Electric Power Generating Companies To Be Discussed

Published on: Wed, 2013-10-02 00:00

ኢትዮጵያ ውስጥ በኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ኩባንያዎች ፈቃድ መስጠት የሚያስችል የሕግ ረቂቅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላከ፡፡ ይህ የሕግ ረቂቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጥቅምት ወር ከሚያፀድቃቸው ሕጎች ተርታ መሰለፉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ ሕጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአይስላንድና በአሜሪካ መቀመጫውን ካደረገ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ ኩባንያ ጋር የኃይል ግዥ ስምምነት ሰሞኑን ተፈራርማለች፡፡

ለ30 አገሮች የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለቤት የሆነው ሬክጃቪክ የተሰኘው ግዙፍ ኩባንያ በአራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ከጂኦተርማል አንድ ሺሕ ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ጣቢያ ይገነባል ተብሏል፡፡

ገንዘቡን መቀመጫውን ካደረገባቸው አገሮችና ካናዳ ውስጥ ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት እንደሚያገኝ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ይህ ኩባንያ የሚያመነጨውን ኃይል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለመግዛት ውል ገብቷል፡፡ ውሉ ለ25 ዓመት የሚቆይ መሆኑም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሚረከበውን የኤሌክትሪክ ኃይል እንደ ሁኔታው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርበው ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሥራ ዋነኛ ባለቤት መንግሥታዊው የልማት ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ነው፡፡ በርካታ አገሮች በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ቢያሳዩም፣ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያ ክፍት ማድረግ የሚያስችል ሕግ ባለመኖሩና መንግሥትም ዘርፉን ክፍት ለማድረግ ፍላጎት ባለማሳየቱ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይተዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ምንጮች እንደገለጹት የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የአሜሪካና የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጥያቄያቸውን ለመንግሥት አቅርበው የዚህን ሕግ መፅደቅ እየተጠባበቁ ነው፡፡

በሕግ ረቂቁ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ከሚሆነው የኃይል ማመንጫ ንዑስ ዘርፎች መካከል ንፋስና ጂኦተርማል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መንግሥት በውኃ ኃይል ማመንጨት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ለጊዜው በሩን ክፍት ማድረግ አለመፈለጉ ታውቋል፡፡
Source: The Reporter



Main menu 2

Lambadi Software Developer P.L.C