Diyajo Expansion Project Is Underway With 50 million $
ዲያጆ በ50 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ ነው
በአዲስ አስተሻሸግ ያቀረባቸውን የሜታ ቢራ ምርቶች ወደገበያ አስገባ
የእንግሊዙ ዲያጆ ኩባንያ ከ11 ወራት በፊት የገዛው ሜታ አቦ ቢራ አክሲዮን ማኅበር፣ በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ምርቴን በእጥፍ ያሳድግልኛል ያለውን የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ፋብሪካው በአዲስ አስተሻሸግ ያቀረባቸውን ሁለት የቢራ ምርቶች ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ እንደተጠቀሰው፣ ሜታ ቢራ በገበያ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት የበለጠ ለማሳደግ ዲያጆ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ወደፊትም እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
ዲያጆ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ከተረከበ ከ11 ወራት በፊት ለፋብሪካው ግዥ ካወጣው 225 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ፣ 50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቀውን የመጀመሪያው የሆነውን የማስፋፊያ ሥራ በመጪው ዓመት ለማጠናቀቅ ማቀዱንም የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
ናይጄሪያዊው የፋብሪካው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ፍራንሲስ አግቦኒሆር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የማስፋፊያ ሥራው የፋብሪካውን የማምረት አቅም በእጥፍ ከማሳደጉም በላይ፣ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ምርቶች የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኙ በሚያስችሉ የጥራት ደረጃዎች ምርቶችን ለማቅረብ ይረዳዋል፡፡
የፋብሪካው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሪት ሶሎሜ ወንድወሰን በበኩላቸው፣ ለማስፋፊያ ሥራው የሚያስፈልጉ ትላልቅ ዕቃዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ነው ብለዋል፡፡ የማስፋፊያ ግንባታውን በቶሎ ለመጨረስ እየተሠራ መሆኑንና በመጪው ዓመት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ አሁን በማምረት ላይ ያለው የቢራ መጠን ምን ያህል እንደሆነና የማስፋፊያ ሥራው ምርቱን ምን ያህል እንደሚያሳድገው አኀዛዊ መረጃ ለመስጠት ያልፈለጉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ በደፈናው የማስፋፊያ ሥራው የሜታን ምርት በእጥፍ ያሳድገዋል ማለትን መርጠዋል፡፡
ዲያጆ ፋብሪካውን ከተረከበ በኋላ የገበያ ድርሻቸውን ምን ያህል እንደደረሰ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ “ይህንን ያህል ነው ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ፤” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት አሁን ያሉት መረጃዎች በግልጽ የተቀመጡ ባለመሆናቸው የገበያ ድርሻው ይህንን ያህል ነው ለማለት እንደሚከብዳቸው ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩልም በኢንዱስትሪው አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እየተካሄዱ በመሆኑ የገበያውን ድርሻ ይህንን ያህል ነው ብሎ ለማለት የሚያስችል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
“ሆኖም በኢትዮጵያ የቢራ ገበያ አለ፡፡ የተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፤” ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ የፋብሪካቸው አካሄድ ስትራቴጂካዊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዲያጆ ከሚያካሄደው ኢንቨስትመንት ጀርባ ኅብረተሰቡን የማገልገል ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው ብለው፣ ድርጅቱ ኢንቨስት በሚያደርግባቸው አገሮች ሁሉ ይህንን ዓላማውን ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የአፍሪካውያን ተፈጥሮያዊ ሀብት ሳይዛባ እንዲቀጥልና፣ የተሻለ ዜጋ ማፍራት እንዲችል ሜታ ቋሚ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ድርጅቱ ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ከገባበት ጊዜ ወዲህ በዚህ ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባሮችን በመረጃ መልክ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የኢንቨስትመንት ሥራውን እያስፋፉ ለመቀጠልና በደንበኞች ዘንድ ያለው ተቀባይነት እንዲጎላ ለማስቻል፣ በቅድሚያ በሠራተኞቹ ላይ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሠራተኞችን በማብቃትና የተሻለ ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ትልቅ ሥራ ተሠርቷል የሚሉት የድርጅቱ ኃላፊዎች፣ ይህም ወደሚፈልጉት ግብ ለመድረስ ትልቅ መፍትሔ ያስገኛል የሚል እምነት አላቸው፡፡ የሜታ መለያ የሆነው ዓርማ የአንበሳ ምልክት በመሆኑ ይህንኑ ምልክት አጉልቶ ለማሳየትና በሁሉም ዘንድ ምልክቱ እንዲሰርፅ ባለፉት 11 ወራት ብዙ መሠራቱንም ጠቅሰዋል፡፡
በኢንዱስትሪው ውስጥ በሚያደርጉት እንቅስቅሴም ይህ ምልክት የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ መለያ ሆኖ እንዲዘልቅ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አስተሻሸግ ለገበያ የቀረቡት ምርቶች በደንበኞች ዘንድ ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ያመለከቱት ኃላፊዎቹ፣ ምርቱ ይለይባቸዋል ያሉዋቸውንም ምክንያቶች አቅርበዋል፡፡ በተለይ እስካሁን የሜታ ምርትን የበለጠ የሚያጎላው ዓርማ ተደብቆ ነበር የሚሉት የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች፣ አሁን ግን አስተሻሸጉንና የሜታ ቢራ ዓርማ የሆነውን አንበሳና በብርጭቆ ውስጥ የተቀዳ ቢራ የሚያሳየውን ዓርማ በማጉላት የበለጠ ግርማ ሞገስ ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡ በአዳዲስ አስተሻሸግና ዓርማውን በማጉላት ወደ ገበያ የሚገቡ ምርቶችን ለማስተዋወቅ “አንበሳው አገሳ”፣ “ጊዜው የሜታ ነው” የሚሉ መሪ ቃላትን ተጠቅሟል፡፡ በሌላ በኩልም አሁን በገበያ ውስጥ ያሉትና ቀድሞ ሲሠራባቸው የቆዩትን ከአሥር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ጠርሙሶች ደረጃ በደረጃ ከገበያ ለማስወጣት ዕቅድ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡
ዲያጆ ባለፉት አምስት ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ቢዝነስ ከአንድ ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ በማድረግ እያስፋፋ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ከ800 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ታውቋል፡፡
Source:-ethiopianreporter
- 920 reads