Jump to Navigation

Current Low Demand For Construction Machineries Worries Investors

Published on: Sun, 2013-11-24 00:00
Image of construction machineries

የኮንስትራክሽን ማሸነሪዎች ፍላጎት መቀዝቀዝ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ሥጋት መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በኀዳር ወር የኮንስትራክሽን ማሽኖች ኪራይ የሚሟሟቅበት ወቅት መሆኑ ቢታወቅም፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ገበያው ተቀዛቅዞ መቆየቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡

በኮንስትራክሸን ማሽነሪዎች ፍላጎት መቀነስና ከዚሁ ጋር ማሽኖች በስፋት ይከራዩ የነበረበት ዋጋ ማሽቆልቆሉ በዘርፉ ለተሰማሩት ተዋናዮች አስደንጋጭ ክስተት መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

በማሽነሪዎች ፈላጊ ማጣትና ለኪራይ ዋጋውም መውረድ ሦስት ነጥቦች በምክንያትነት እየተነሱ ነው፡፡ የመጀመሪያው በርካታ ነጋዴዎች በቂ ጥናት ሳያደርጉ ወደ ዘርፉ መግባታቸው፣ ሁለተኛው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተለየዩ ማሽነሪዎችን እያገጣጠመ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ማቅረቡ፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥት በዚህ ዓመት አዳዲስ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን አለመጀመሩ እንደ ምክንያት ተነስተዋል፡፡

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ በርካታ ባለሀብቶች የኮንስትራክሽን ማሽኖችን ከውጭ አገር፣ በተለይም ከስፔን ወደ አገር ውስጥ ማስገባታቸውን መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ በየዓመቱ ከሦስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶች አሥር ሺሕ የሚደርሱ ማሽነሪዎች ባለቤት በመሆን ለኪራይ ገበያ ማቅረባቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስከ ኀዳር ወር 2006 ዓ.ም. ድረስ ስለኮንስትራክሸን ማሽነሪዎች ፈላጊ ማጣት የሚያነሳ ባለሀብት ባይኖርም፣ በጥቅምትና በኀዳር ወራት ማሽኖቻቸው ያለሥራ የተቀመጡባቸው ባለሀብቶች ጉዳዩን ማብላላት ይዘዋል፡፡

ለኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ገበያ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገበያው ከሚፈልገው በላይ ብዛት ያላቸው ማሽኖች ገብተዋል ይላሉ፡፡ ይህም የዋጋ መውረድ ከማስከተሉም በላይ አብዛኛዎቹ ማሽን አከራዮች ያለሥራ እንዲቀመጡ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡

በዚህ ሐሳብ በተወሰነ ደረጃ ተሰማምተው፣ ነገር ግን የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ለግሉ ዘርፍ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ፍላጎት መቀዝቀዝ የማይናቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን በአመዛኙ የሚቀበሉም አሉ፡፡ እነዚህ የዘርፉ ተዋናዮች ኮርፖሬሽኑ ቀላልና ከባድ ማሽነሪዎችን በማምረት ለክልል የገጠር መንገድ ኤጀንሲዎች፣ ለክልል ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዞች፣ እንዲሁም ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እያቀረበ በመሆኑ የግል ማሽን አከራዮች ገበያ እንዲቀዘቅዝባቸው ምክንያት ሆኗል በሚለው ይስማማሉ፡፡

ምክንያቱም ትልልቆቹ የማሽን ተጠቃሚዎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በመሆናቸውና እነዚህ የልማት ድርጅቶች የራሳቸው ማሽን ካላቸው የግል ዘርፉን ማሽነሪዎች የሚፈልጉበት ምክንያት አይኖርም ሲሉ ገበያው የቀዘቀዘበትን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡

ሁሉም ማሽን አከራዮች በዋናነት የሚስማሙበት ነጥብ በ2006 በጀት ዓመት መንግሥት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ባለመጀመሩ ገበያውን እንዳቀዘቀዘው ነው፡፡

መንግሥት በ2005 ዓ.ም. የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ለማሳካት 20 ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በ2006 ዓ.ም. በአምስት ቢሊዮን ብር ቀንሶ 15 ቢሊዮን ብር ፀድቋል፡፡ ይህ ገንዘብ ለሁሉም ክልሎች ሲከፋፈል የሚያንስ ከመሆኑም በላይ፣ ፕሮጀቶቹ ባለፈው በጀት ዓመት የተጀመሩና ሥራዎቹ በዚያ ጊዜ የተያዙ በመሆኑ በዚህ ዓመት አዳዲስ የኮንስትራክሸን ማሽነሪዎችን ላይቀበሉ ይችላሉ የሚል ነው፡፡

በሌላ በኩል በ2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከተያዘለት 20 ቢሊዮን ብር ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች መያዙ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ፍላጎቱን አቀዝቅዞት ሊሆን እንደሚችል፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ንጉሤ እምነታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
Source: The ReporterMain menu 2

Lambadi Software Developer P.L.C