Jump to Navigation

Construction Of Meles Zenawi Memorial Refferal Hospital Completed

Published on: Tue, 2013-11-26 00:00
Image of Meles referral hospita in Jijiga

በሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ የተገነባው የመለስ መታሰቢያ ሪፈራል ሆስፒታል የግንባታ ስራው ተጠናቀቀ።

ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሆስፒታሉ ከ5 ሚሊየን ለሚልቁ የክልሉና አጎራባች አገራት ዜጎች የህክምና አገልግሎት የመስጠት አቅም አለው።

የሆስፒታሉ መገንባት የክልሉ ዜጎች ወደ አዲስ አበባ እና የውጭ ሃገራት የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጉዞና ዕንግልት እንዲሁም አቅም የሌላቸው የክልሉ ነዋሪዎች በህክምና እጦት ምክንያት የሚደርስባቸውን የጤና ቀውስ ያስቀራል ተብሏል።

የሆስፒታሉን አገልግሎት መጀመር በጉጉት የሚጠባበቁት የክልሉ ነዋሪዎችም ከዚህ ቀደም በህክምና መርጃ መሳሪያዎች አገልግሎት ያለመኖር ሳቢያ ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ሐገራት አቅም ያለው ብቻ ይታከም እንደነበር በማስታወስ አሁን ግን ይህ ሆስፒታል ስራውን ሲጀምር ችግሩን ያስቀርልናል ይላሉ።

ባለ ሁለት ህንፃው የመለስ መታሰቢያ ሪፈራል ሆስፒታል ከህንፃው አናት ላይ 3 ሄሊኮፕተሮችን ማሳረፍ የሚያስችል ቦታ ተዘጋጅቶለታል።

ከዚህም በተጨማሪ በህንፃው ውስጥ ለአካል ጉዳተኞችና ህሙማን በጋራ የሚጠቀሙበት መንገድና 19 ሰዎችን በአንዴ መጫን የሚችሉ 4 አሳንሱሮች ተገጥመዋል።

ህሙማን ተኝተው የሚታከሙበት 700 አልጋዎችን የያዘ ሲሆን፥ በአንዴ 500 ሰዎች ተኝተው መታከም የሚችሉበትም ነው።

ወደ ሆስፒታሉ የሚገባን አቧራና ከሆስፒታሉ የሚወጣውን ሽታ መምጠጥና በንፁህ አየር መሙላት የሚያስችል ዘመናዊ መሳሪያም ተገጥሞለታል።

የክልሉ የጤና ቢሮ የምህንድስና ክፍልና የመለስ ፋውንዴሽን ግንባታ ክትትል ሃላፊ እድሪስ ኡስማን፥ እንደ ሪፈራል ሆስፒታል ሊያሟላ የሚገባውን ማንኛውም መሳሪያዎች ሊይዝ ይገባል ከሚል ጥናት መነሻነት ወደግንባታው መገባቱን ይናገራሉ።

አቶ እድሪስ ሙሉ በሙሉ የክልሉ መንግስት ወጪ የተገነባው ሆስፒታሉ፥ የውስጥ የህክምና ቁሳቁሶችን ለሟሟላት የክልሉ ነዋሪዎችና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል ብለዋል።

በሆስፒታሉ ድንገት የኤሌክትሪክ መቋረጥ ቢያጋጥም ለ7 ሰዓት የኤሌክትሪክ ሃይልን ይዞ መቆየት የሚችል መሳሪያም መገጠሙን የሚናገሩት አቶ እድሪስ፥ የንፁህ ውሃ ፍላጎቱንም በግቢው ውስጥ ከተቆፈረ ጉድጓድ በሚወጣው ውሃ ሙሉ በሙሉ መጠቀም የሚያስችለው ስራም ተሰርቷል ብለዋል።

የመለስ መታሰቢያ ሪፈራል ሆስፒታል 3 ዓመት ተኩል የግንባታ ጊዜን ወስዷል።
Source: Fana Broadcasting Corporate (FBC)



Main menu 2

Lambadi Software Developer P.L.C