Jump to Navigation

Construction Of 50 Thousand Condos To Commence In Addis Next January

Published on: Tue, 2013-12-03 00:00
Image showing condomium building

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በመጪው ጥር ወር 50 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሊጀመር ነው ።

በአዲስ አበባ በዘንድሮው በጀት ዓመት 67 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ፥ 50 ሺህ የ20/80 ፤ 12 ሺህ የ40/60 እንዲሁም 5 ሺህ የህብረት ስራ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ናቸው ግንባታቸው የሚጀመረው።

የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታን የሚያካሂደው የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት፥ 50 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል 400 ሄክታር መሬት መረከቡን ገልጿል ።

የስራ ተቋራጮችን ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትንና በግንባታ ስራው ተሳታፊ አካላትን የመለየት ስራው እየተከናወነ እንደሆነና የፊታችን ጥር ወር ላይ ሙሉ በሙሉ የ50 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ እንደሚጀመር የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ በፍቃዱ አሰፋ ተናግረዋል።

የቤቶቹን ግንባታ በጥራትና በፍጥነት ለማከናወንም የካይዘን ፍልስፍና ስልጠና በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለሚሳተፉ ከ500 በላይ የስራ ተቋራጮች ፣ ለግብዓት አቅራቢ የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራቶችና ለፅህፈት ቤቱ ሰራተኞች መሰጠቱን ምክትል ስራ አስኪያጁ አስታውሰዋል።።

ባለፈው ዓመት በየካ አባዶ ሳይት ግንባታቸውን በሚያካሂዱ ሁለት የፕጀክቶች ላይ ተሞክሮ ውጤት ያስገኘው ይኸው ፍልስፍና በቀጣይም በበርካታ ሳይቶች ላይ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ስራም ይከናወናል ብለዋል።

የካይዘን ፍልስፍና ተግባራዊ መደረግ ከዚህ ቀደም አንድ ህንፃን ለመገንባት ይወስድ የነበረውን ከ2 አስከ 3 ዓመት የሚደርስ የጊዜ ቆይታን ፤ ከ10 ወር አስከ አንድ አመት የሚያወርድና የግብዓት ብክነትን የሚከላከል ፣ ጥራትን የሚያረጋግጥና ወጪን የሚቀንስም ይሆናል።

የመሰረተ ልማት ተቋማት ከፅህፈት ቤቱ ጋር በቅንጅት መስራት የሚያስችላቸውን ስራ እንዲያከናውኑም በከንቲባ ድሪባ ኩማ በሚመራ ግብረሃይል አስፈላጊው ክትትልና የማስተካከያ ስራም ይሰራል ነው ያሉት አቶ በፍቃዱ።

በተያዘው በጀት ዓመት የሚጀመሩት የ50 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከ30 እስከ 40 በመቶ የግንባታ ሂደታቸው በበጀት ዓመቱ የሚከናወን ሲሆን ፥ የዛሬ አመት ጥር ወር ላይም ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሏል።

አሁን በግንባታ ላይ የሚገኙት 95 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታም እስከ ሰኔ ወር ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ።
Source: Fana Broadcasting Corporate(FBC)



Main menu 2

Lambadi Software Developer P.L.C