Condo Lottery To Be Postponed
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እያስገነባቸው ከሚገኙት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውሰጥ፣ ከ17 ሺሕ በላይ የሚሆኑት እስከ ኅዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ ለነባር ተመዝጋቢዎች፣ በተለይ ባለአንድ መኝታና ስቱዲዮ ተመዝጋቢዎች በሙሉ በዕጣ እንደሚሰጡ የተነገረ ቢሆንም፣ ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ነዋሪው የቤት ኪራይ አማሮት የኮንዶሚኒየም ዕጣ መውጫውን ቀን እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት፣ ‹‹ዕድሌ ይረዳኝ ይሆን? ለልማት ተነሺዎች የሚሰጠው ቤት ዕድሌን ያጣብብብኝ ይሆን?›› በማለት ከራሱ ጋር እየተሟገተ ባለበት ሁኔታ፣ የዕጣ ማውጫው ቀን መራዘሙ ተስፋ ከማስቆረጥም ባለፈ ግራ የሚያጋባ እንደሆነ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
እንደ ምንጮቹ ገለጻ ከሆነ፣ ጽሕፈት ቤቱ የዕጣ ማውጫውን ጊዜ ለጥር 30 እና ሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. አስተላልፎታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወደ ሥራ የተገባው ከታሰበበት ጊዜ ተዘግይቶ በመሆኑ፣ ዕጣ የሚወጣበት የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ 80 በመቶ መጠናቀቅ ሲገባው ከዛ በታች በመሆኑ የዕጣ ማውጫውን ቀን ለማራዘም መገደዱን ተናግረዋል፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በአራት ኪሎ፣ ቱሉዲሞቱ ወይም ፕሮጀክት 11 እና 12 በሚባለው ሳይት፣ በቂሊንጦና በሌሎችም አካባቢዎች በመገንባት ላይ እንደሚገኙና የተወሰኑት በተፋጠነ ሁኔታ እየተሠሩ መሆኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እየተገነቡ ስለሚገኙት የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ሁኔታና የዕጣ ማውጫ ጊዜ ለምን ማራዘም እንደተፈለገ ማብራሪያ እንዲሰጡን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊውንም ሆነ ከፍተኛ ኃላፊዎችን ለማግኘት ደጋግመን ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን ባለመቻሉ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በሞዴልነት እንዲወሰድ በሚል እስከ 12 ፎቅ የሚደርስ የጋራ መኖሪያ ቤት ባስገነባበት ልደታ ሳይት የተዘረጋው የውኃ መስመር ውኃ ማስተላለፍ ባለመቻሉ፣ ሌላ መስመር በመዘርጋትና በፎቆቹ መጨረሻ ጣሪያ ላይ በሮቶ በመሙላት ለማከፋፈል እየተሞከረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ መስመሩን የዘርጋው ኮንትራክተርም ሙሉ ክፍያ ሳይፈጸምለት መባረሩን ባለዕድሎች ተናግረዋል፡፡
Source: The Reporter
- 1668 reads