Jump to Navigation

Bill To Encourage Private Electric Generation Approved

Published on: Wed, 2013-11-20 00:00
Image of Elecric cables

የግል ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትና በመሸጥ ኢንቨስትመንት ውስጥ በስፋት እንዲገቡ የሚያበረታታውን የኢትዮጵያ የኢነርጂ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ማክሰኞ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔው አፀደቀ፡፡

የፀደቀው የኢነርጂ አዋጅ በ1989 ዓ.ም. የወጣውንና በአሁኑ ወቅት አገሪቱ እየጠቀመችበት ያለውን የኤሌክትሪክ አዋጅ የሚተካ መሆኑ በፓርላማው ጉባዔ ላይ ተገልጿል፡፡ በሥራ ላይ የሚገኘው የኤሌክትሪክ አዋጅ ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት አንፃር ከአገር አልፎ አኅጉራዊ ትስስርን መፍጠር ተገቢና ጠቃሚ ከሆነበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ፣ በአዲሱ የኢነርጂ አዋጅ መተካት እንዳለበት ምክር ቤቱ ተግባብቶበታል፡፡ የፀደቀው የኢነርጂ አዋጅ በቀድሞው አዋጅ መሠረት ተቋቁሞ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኤጀንሲ አወቃቀር ላይ ለውጥ በማድረግ በቦርድ እንዲተዳደርና ስያሜውም የኢትዮጵያ የኢነርጂ ባለሥልጣን እንዲባል ደንግጓል፡፡

ይህ ባለሥልጣን በቀድሞው አዋጅ መሠረት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተግባር ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት ቢኖረውም፣ በመንግሥት ከተቋቋመው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ውጪ ከኤጀንሲው ፈቃድ በመውሰድ በኃይል የማመንጨትና የመሸጥ ሥራ የገቡ የግል ኩባንያዎች በጣት የሚቆጠሩና በአቅምም አነስተኛ ናቸው፡፡ በመሆኑም የግል ኩባንያዎች በዚህ የኃይል ማመንጨትና መሸጥ ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት እንዲገቡ ማበረታታትና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር በአዋጁ እንዲካተት ተደርጎ ኃላፊነቱም በአዲስ ለሚዋቀረው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ተሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለንግድ ዓላማ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ ማስተላለፍ፣ ማከፋፈልና መሸጥ፣ ወደ ውጭ አገር መላክ ወይም ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንዲሁም ሌሎች ከኃይል ጋር የተያያዙ እንደ የኃይል አገልግሎት ተቋራጭነትና የማማከር ተግባርና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ድርጅቶች ፈቃድ የመስጠት መብት በአዋጁ ተሰጥቶታል፡፡

ባለሥልጣኑ ፈቃድ ለመስጠት ብቁ የሚያደርጉ መመዘኛዎችን በደንብ እንዲያወጣ ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፣ በዘርፉ ለመሳተፍ የሚያስችል የገንዘብ ምንጭ፣ የቴክኒክ ችሎታ፣ ሙያና ልምድ የመሳሰሉት መረጋገጣቸው መሠረታዊ መመዘኛዎች ናቸው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በተለይም ከውኃ ኃይል የማመንጨት ሥራ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ነዋይን፣ የቴክኒክ ብቃትና የሙያ ተሞክሮን ስለሚጠይቅ እንዲሁም ሰፊ ጊዜን የሚወስድ በመሆኑ፣ የግል ባለሀብቶችን ትኩረት ያላገኘና የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ሆኖ እንደቆየና ይህንን መቅረፍ እንደሚገባ የአዋጁ አስፈላጊነትን የሚገልጸው አባሪ ማብራሪያ ሰነድ ያስረዳል፡፡

በመሆኑም በዚህ ከፍተኛ የኃይል ማመንጨት ተግባር የግል ባለሀብቶች እንዲሳተፉና ያመረቱትን ኃይል ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን መሸጥ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታና ማበረታቻ በአዋጁ እንዲካተት መደረጉን ማብራሪያው ይገልጻል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥራ ከሚጠይቀው የኢንቨስትመንት ወጪ በተጨማሪ በባህሪው ለተለያዩ አደጋዎች የተጋለጠ በመሆኑ፣ የግል ኩባንያዎችን ትኩረት እንዳላገኘ የሚያትተው የአዋጁ ማብራሪያ የግል ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ በመግባት የሚያመነጩትን ኃይል የሚገዛው የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በሚያጋጥሙት የተለያዩ ችግሮች ግዢውን ቢያቋርጥ የሚለው ሥጋት ደግሞ ሌላው የግል ኩባንያዎችን ያሸሸ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ያስረዳል፡፡

ይህንን ችግር የመቅረፍና ለግል ኩባንያዎች ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ኃላፊነት በአዲሱ አዋጅ ለሚቋቋመው የኢነርጂ ባለሥልጣን ተሰጥቷል፡፡ ከኃላፊነቶቹ መካከል የግል ኩባንያዎች በኃይል የማመንጨት ተግባር ተሰማርተው የሚያመነጩትን ኃይል ለኮርፖሬሽኑ በሕጋዊ የሽያጭ ውል እንዲያስተላልፉ ማድረግ፣ ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ችግሮች ውሉን ቢያቋርጥ በኩባንያዎቹ ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ፣ የባለሥልጣኑ ጥናትን መሠረት ያደረገ ትንተና በመሥራት ኩባንያዎቹ ለሚገቡት የኃይል ሽያጭ ስምምነት ከመንግሥት ሉዓላዊ ዋስትና እንዲያገኙ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባለሥልጣኑ የኤሌክትሪክ ታሪፍን በራሱ እንዲወስን በአዋጁ ሥልጣን ተሰጥቶትል፡፡ ባለሥልጣኑ ታሪፍ የመወሰን ኃላፊነት የተሰጠው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያ ግሪድ (ኔትወርክ) ውጪ ባሉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች አማካይነት ለሚተላለፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡

ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ውጪ ያሉ መስመሮችን የሚጠቀሙት የግል የኃይል አመንጪዎች በመሆናቸው ከሚጠቀሙት የኃይል ምንጭ ዓይነት፣ የቦታ አቀማመጥ፣ የገንዘብ ውድነት፣ ውል የተደረገባቸው ልዩ ሁኔታዎችንና ሌሎች ሁኔታዎችን በማጥናት ታሪፉን እንዲወስን ለባለሥልጣኑ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለውን ብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያ ግሪድ ታሪፍ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከት በመሆኑ በባለሥልጣኑ አቅራቢነት በመንግሥት ይወስናል፡፡
Source: The ReporterMain menu 2

Lambadi Software Developer P.L.C