Jump to Navigation

Aba Samuel Hydropower To Be Renewed With 296 mln Birr

Published on: Wed, 2013-11-06 00:00
Image of Aba Samuel ,the first hydro power station in Ethiopia

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሆነው አባ ሳሙኤል ከቻይና መንግሥት በተገኘ 16 ሚሊዮን ዶላር (296 ሚሊዮን ብር) ዕድሳት ሊደረግለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የአባ ሳሙኤል ኃይል ማመንጫ ጣቢያን እንዲያድስ ኃይድሮ ቻይና ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ድርድር እያካሄደ መሆኑን፣ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ለማ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሆነው አባ ሳሙኤል እያመነጨ የሚገኘው የኃይል መጠን ሦስት ሜጋ ዋት ብቻ ነው፡፡ በሚካሄደው ዕድሳት ጣቢያው ኃይል የማመንጨት አቅሙ በእጥፍ እንደሚጨምር (ስድስት ሜጋ ዋት) ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የእደሳ ሥራው የግድቡን መዋቅር ጨምሮ በመበከሉ ምክንያት ጥቅም መስጠት የማይቻለውን የግድቡን ውኃ ማስወገድ፣ ለመልሶ ግንባታው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን ዲዛይን አድርጐ ማምረት፣ ማቅረብና ግንባታውን ማካሄድ ያጠቃልላል፡፡

የአባ ሳሙኤል ኃይል ማመንጫ ግድብ በ1931 ዓ.ም ሥራ መጀመሩ ይነገራል፡፡ እስከ 1962 ዓ.ም ድረስ ጣቢያው ኃይል ሲያመነጭ ቢቆይም በመሣሪያዎች እርጅና ምክንያት ሥራ አቁሞ ነበር፡፡ በተወሰነ ደረጃ ጥገና እየተደረገለት ሦስት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶ ለብሔራዊ ኃይል ሥርጭት መመገቡን ቀጥሏል፡፡

የአባ ሳሙኤል ግድብ በ1,495 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ፈጥሯል፡፡ ወደዚህ ሐይቅ ከአዲስ አበባ የሚነሱት ትንሹና ትልቁ አቃቂ ወንዞች ይገባሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ወንዞች በኢንዱስትሪ ፍሳሽ የተበከሉ በመሆናቸው የአባ ሳሙኤል ግድብ ለከፍተኛ ብክለት ተጋልጧል፡፡

ነገር ግን ሁለቱ የአቃቂ ወንዞች ከብክለት ታቅበው የአባ ሳሙኤል ሐይቅ እንዲያገግም በርካታ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ አቶ መኩሪያ እንዳሉት የእድሳት ሥራው ለአካባቢ ጥበቃ ጥሩ አጋጣሚ ከመሆኑም በላይ ግድቡ ታሪካዊ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 29 ቀን 2001 ዓ.ም. የኢንዱስትሪ ብክለት መከላከያ ደንብ አውጥቷል፡፡ ይህ ደንብ ነባር ፋብሪካዎች እስከ ታኅሳስ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ከብክለታቸው እንዲገቱና በንፁህ የማምረት ዘዴ እንዲጠቀሙ ቀነ ገደብ ሰጥቷል፡፡

ደንቡ የሰጠው ጊዜ ከሁለት ወር በኋላ ታኅሳስ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ የሚያበቃ በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በበካይ ፋብሪካዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ በዚህ ዓመት በ55 ፋብሪካዎች ላይ ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
Source: The Reporter



Main menu 2

Lambadi Software Developer P.L.C