Jump to Navigation

መንገዶች ባለሥልጣንና ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በባቡር ሐዲድ ማቋረጫ ላይ አልተግባቡም

Published on: Tue, 2014-04-15 16:40

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በመዘርጋት ላይ ባለው ቀላል የባቡር መስመር ምድር ለምድር በተዘረጋው ሐዲድ ላይ እግረኞች አቋርጠው እንዲያልፉ በመታሰቡ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን አግባብ አይደለም አለ፡፡

በአብዛኛው ሥራ ላይ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ተግባብተውና ብዙ ሥራዎችን አብረው እየሠሩ መሆኑን የገለጹት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ፣ በረጅም ርቀት ምድር ለምድር እየተዘረጋ ያለው የቀላል ባቡር ሐዲድ፣ በድልድይ ላይ ቢያልፍ የተሻለና የባለሥልጣኑም እምነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ዋና ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ፣ የተቀላጠፈና ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት መሆኑን ጠቁመው፣ የእግረኞች ማቋረጫን በሐዲዱ ላይ ማድረግ የታሰበውን ዓላማ እንዳይመታ ያደርገዋል የሚል ፍራቻ ስላላቸው ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ምድር ለምድር በሚዘረጋው ሐዲድ በተወሰኑ ርቀቶች ላይ ለመንገደኞች ማቋረጫ የሚሆን መሸጋገሪያ እንደሚሠራና ባቡር መምጣቱን የሚጠቁም የትራፊክ መብራት ምልክት (ሲግናል) እንደሚኖር የተገለጸ ቢሆንም፣ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ‹‹ባለሙያ መሐንዲስ እንደመሆኔ፣ ይህ አሠራር የትራፊክ መጨናነቅ ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ እምነት ለሕዝቡም ሆነ ለባቡሩ ፍጥነት ማቋረጫው ወይም የባቡሩ ሐዲድ በድልድይ ቢሆን ይመረጣል፡፡ አሁን እንኳን በሰዓት ተወስኖ በተተከለ የትራፊክ መብራት ላይ ያለውን መጨናነቅ መመልከት እንችላለን፤›› በማለት፣ እግረኞች እንዲያቋርጡበት የታሰበው የሐዲድ መስመር አግባብ አለመሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ከአራዳ ጊዮርጊስ በአውቶብስ ተራ፣ ጎጃም በረንዳ፣ በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት እስከ አውቶብስ ተራ፣ ከዚያም በሰባተኛ፣ በአብነት አድርጐ ልደታ ፍርድ ቤት፣ እንዲሁም ከሲኤምሲ በመገናኛ፣ በዑራኤልና በመስቀል አደባባይ በማድረግ ልደታ ፍርድ ቤት ላይ ተገናኝቶ እስከ ጦር ኃይሎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከመስቀል አደባባይ እስከ ቃሊቲ በመዘርጋት ላይ የሚገኘው የቀላል ባቡር ሐዲድ ግንባታ 60 በመቶ ሥራው መጠናቀቁን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስረድተዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዶ/ር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩ ሚያዝያ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከባለድርሻ አካላት ጋር በግዮን ሆቴል ለግማሽ ቀን በተደረገ ውይይት ላይ እንደገለጹት፣ የቀላል ባቡር ሐዲድ ግንባታው በፍጥነት እየተሠራና በሚያዚያ ወር 2007 ዓ.ም. ሥራው ተጠናቆ የሙከራ ሥራ ይጀምራል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኮርፖሬሽኑ የሚያስጨንቀው የሐዲድ ዝርጋታው ሳይሆን፣ ሕዝቡ ፕሮጀክቱን ‹‹የኔ ነው›› ብሎ የሚጠቀምበትን ሁኔታ ማመቻቸት ብቻ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ባቡሩ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ወጣት ኢትዮጵያውያን ሥልጠና ማግኘት ስላለባቸው፣ ከ200 በላይ የባቡር ሾፌሮች፣ የሐዲድ መካኒኮችና ሌሎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያጠኑ ለ11 ወራት ቆይታ ወደ ቻይና መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ባቡሩ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ኮርፖሬሽኑ ተሠርተው መጠናቀቅ ያለባቸውን የተለያዩ ሥራዎች ማለትም የእግረኞች ማቋረጫና መሳፈሪያ ጣቢያዎች፣ ተሽከርካሪ ማዞሪያዎች (በአማካይ 800 ሜትር ያህል ከነዱ በኋላ የሚታጠፉበት) ታሳቢ ማድረጉን የገለጹት ዶ/ር ጌታቸው፣ አሥር የባቡር መነሻ ጣቢያዎችና 39 ፌርማታዎች እንደሚገነቡ አስታውቀዋል፡፡ ፌርማታዎቹ በተነገቡበት ቦታ ሁሉ የእግረኛ ማቋረጫዎች ድልድዮችም እንደሚኖሩና አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

የባቡር ሐዲድ ግንባታው እየተጠናቀቀ በመሆኑ ከግንባታው ጎን ለጎን የባቡር ሥራውም እየተከናወነና እየተገጣጠመ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በመሠራት ላይ ያሉት ባቡሮች 64 መቀመጫዎች እንደሚኖሩዋቸውና ባጠቃላይ ከ280 በላይ ተሳፋሪዎችን በአንድ ጊዜ እንደሚይዝ ገልጸዋል፡፡ ለማያዩ የድምፅ፣ ለማይሰሙ የምልክት ማስረጃዎችንም የያዘ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ባቡሩ ሥራ ሲጀምር የራሳቸው ተሽከርካሪ ያላቸው ሰባት በመቶ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀላል የባቡር ትራንስፖርት ሙሉ በሙሉ ችግር ይፈታል ማለት ሳይሆን፣ ያለውን መጨናነቅ ለመቅረፍና የተሻለ ትራንስፖርት ወዳለበት ጣቢያ ለመድረስ ፈጣንና ተመራጭ መሆኑን ዶ/ር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

ከፌርማታዎቹ መጨረሻ ከ400 ሜትር በላይ ተጉዘው ለሚኖሩ ነዋሪዎችና በየፌርማታው ወርደው ወደ ሌሎች አቅጣጫዎች ለሚጓዙም የመካከለኛ አውቶብስ ትራንስፖርት ለማዘጋጀት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ይኼ የሚደረገው ግን  ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን በማይነካና ሥራቸውን በማይሻማ ሁኔታ መሆኑን አውስተዋል፡፡

እየተፋጠነ የሚገኘው የቀላል ባቡር ሐዲድ ዝርጋታ ፕሮጀክት፣ ባለቁ ባለቁ ግንባታዎች ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መዘርጊያ ምሰሶዎች እየተተከሉ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኬብሎች ዝርጋታ ሥራ መጀመሩም ታውቋል፡፡Main menu 2

Lambadi Software Developer P.L.C